ወጋገን ባንክ ከነበረበት ዝቅተኛ አፈፃፀም ወጥቶ ብር 1.4 ቢሊዮን አጠቃላይ ትርፍ አስመዘገበ

ወጋገን ባንክ ከነበረበት ዝቅተኛ አፈፃፀም ወጥቶ ብር 1.4 ቢሊዮን አጠቃላይ ትርፍ አስመዘገበ

አዲስ አበባ፣ሐምሌ 22 ቀን 2014 ዓ.ም- ወጋገን ባንክ እ.ኤ.አ ሰኔ 30 በተጠናቀቀው የ2021/22 የበጀት ዓመት ከነበረበት ዝቅተኛ አፈፃፀም ወጥቶ 1.4 ቢሊዮን አጠቃላይ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡ ወጋገን ባንክ ይህንን ውጤት ያስመዘገበው የባንኩ የስራ አመራር ቦርድ አባላት፣ባለአክሲዮኖች ማኔጅመንት እና ሰራተኞች ባንኩን ወደ ትርፋማነት ለመመለስ ባከናወኑት የተቀናጀ ጥረት እና ርብርብ መሆኑን የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አክሊሉ ውበት አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትና ባለአክሲዮኖች በየጊዜው እየተገናኙ በቅርበት በመስራት የባንኩን እውነተኛ ገፅታ ደንበኞችና አጠቃላይ ማህበረሰቡ እንዲገነዘቡት በማድረጋቸው ቀደም ሲል ባንኩ ላይ በተሳሳተ መረጃ ላይ ተመርኩዞ የደረሰበት የስም ማጥፋት ወደቀደመ መልካም ስሙ እንዲመለስ እንዲሁም ደንበኞች ያላቸው መተማመን ተመልሶ ከባንኩ ጋር እንዲሰሩ በማስቻሉ ባንኩ የተሻለ አፈፃፀም እንዲያስመዘግብ አስተዋፅኦ ማድረጉን ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል፡፡
አቶ አክሊሉ አክለውም እ.ኤ.አ ሰኔ 30 2022 በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ወጋገን ባንክ ያስመዘገበው ትርፍ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ከተከሰተው ግጭት ጋር ተያይዞ በክልሉ የነበሩት 112 ቅርንጫፎች አሁንም ድረስ ተዘግተው ባሉበት እና በ288 ቅርንጫፎቹ ብቻ አገልግሎት እየሰጠ ከመሆኑ አንጻር ትልቅ እመርታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ባለፈው የበጀት ዓመት ብር 40 ቢሊዮን የነበረው የባንኩ ጠቅላላ ሀብት እ.ኤ.አ ሰኔ 30 2022 በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ወደ ብር 43.6 ቢሊዮን አድጓል፡፡እ.ኤ.አ ሰኔ 30 2022 የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ብር 3.4 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ጠቅላላ ካፒታሉ ደግሞ ብር 6.1 ቢሊዮን ደርሷል፡፡ ባንኩ የሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብም በ2020/21 የበጀት ዓመት ከነበረበት ብር 31.5 ቢሊዮን ሰኔ 30 2022 ወደ ብር 33.9 ቢሊዮን ያደገ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ባለፈው የበጀት ዓመት ብር 27.4 ቢሊዮን የነበረው ለተለያዩ ዘርፎች የሰጠው ብድርም ሰኔ 30 2022 በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ወደ ብር 30.5 ቢሊዮን አድጓል፡፡
ወጋገን ባንክ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት መጋቢት ወር ላይ ተግባራዊ ካደረገው አዲስ የደመወዝ ስኬል በተጨማሪ ከሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለሰራተኞቹ ከአንድ እስከ አራት እርከን የደመወዝ ጭማሪ ያደረገ ሲሆን የአንድ ወር የማትጊያ ክፍያ ሰጥቷል ፡፡
ወጋገን ባንክ ከመጋቢት 2010 እስከ ሐምሌ 2014 ዓ.ም ድረስ ባሉት አራት ዓመታት ብቻ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በመላው ሀገሪቱ ለጤና፣ ለትምህርት እንዲሁም በሰው ሰራሽና ተፈጥሮ አደጋዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በክልሎች እና በፌደራል ደረጃ የተካሄዱ የልማት ሥራዎችን ከብር 72 ሚሊዮን በላይ ወጪ በማድረግ ሲደግፍ ቆይቷል፡፡
ሰኔ 4 ቀን 1989 ዓ.ም በ16 ባለአክሲዮኖች በብር 60 ሚሊዮን የተፈረመ መነሻ ካፒታል እና በብር 30 ሚሊዮን የተከፈለ ካፒታል የተቋቋመው ወጋገን ባንክ በመላው ሀገሪቱ 400 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የባለ አክሲዮኖቹ ቁጥር 5,888 የደረሰ ሲሆን ከ5,000 በላይ ሰራተኞች አሉት፡፡ ወጋገን ባንክ ባለፈው ሰኔ 4 ቀን 2014 ዓ.ም የተመሰረተበትን 25ኛ ዓመት በደመቀ ሁኔታ ማክበሩ ይታወሳል፡፡

About the Author

Comments are closed.