ወጋገን ባንክ “በወጋገን ይቆጥቡ ፣ በወጋገን ይሸለሙ” በሚል ስያሜ ያካሄደው የቁጠባ ማበረታቻ የሎተሪ ዕጣ ወጣ

ወጋገን ባንክ “በወጋገን ይቆጥቡ ፣ በወጋገን ይሸለሙ” በሚል ስያሜ ያካሄደው የቁጠባ ማበረታቻ የሎተሪ ዕጣ ወጣ

አዲስ አበባ ፣ሚያዝያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ፡-ወጋገን ባንክ ከጥቅምት 1 ቀን እስከ መጋቢት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ “በወጋገን ይቆጥቡ፣ በወጋገን ይሸለሙ” በሚል ስያሜ ሲያካሂድ የቆየው የቁጠባ ማበረታቻ የሎተሪ ዕጣ ሽልማት ሚያዝያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም በብሔራዊ ሎተሪ አዳራሽ የወጋገን ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ብርቱካን ገብረእግዚ እና ሌሎች የባንኩ ከፍተኛ የሥራ አመራር አባላት እንዲሁም የብሔራዊ ሎተሪ ኃላፊዎች በተገኙበት ወጥቷል፡፡

ባንኩ የደንበኞቹን የቁጠባ ባህል ለማዳበርና በአጠቃላይ ቁጠባን ለማሳደግ ያዘጋጃቸውና በዕለቱ ዕጣ የወጣባቸው የሽልማት ዓይነቶች 1ኛ ዕጣ አንድ የ2019 ሞዴል ዘመናዊ የቤት መኪና፣ 2ኛ ዕጣ ሁለት ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች፣ 3ኛ ዕጣ 20 የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች፣ 4ኛ ዕጣ 30 ባለ 32 ኢንች ኤል ኢዲ ቴሌቪዥኖች እና 5ኛ ዕጣ 40 ስማርት የሞባይል ስልኮች ናቸው፡፡

በዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የወጋገን ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ብርቱካን ገብረእግዚ ባንኩ “በወጋገን ይቆጥቡ፣ በወጋገን ይሸለሙ” በሚል ስያሜ ያካሄደው የሎተሪ ዕጣ ሽልማት መርሀ-ግብር ደንበኞች የበለጠ ተበረታተው እንዲቆጥቡ በማድረግ ቁጠባን ከማሳደግ እና አዳዲስ ደንበኞችን ከማፍራት እንዲሁም የባንኩን መልካም ገፅታ ከመገንባት አንጻር አበረታች ውጤት ማስገንዘቡን ተናግረዋል፡፡ የአሸናፊ ዕጣ ቁጥሮች በቅርቡ በጋዜጣ የሚወጡ መሆኑን የተናገሩት ወ/ሮ ብርቱካን ባንኩ ለባለዕድለኞች ሽልማታቸውን በሚያዘጋጀው ይፋዊ ሥነ-ሥርዓት ላይ የሚዲያ አካላት በሚገኙበት እንደሚያስረክብ ተናግረዋል፡፡

ወጋገን ባንክ በ2012 ዓ.ም ባካሄደው “ከወጋገን ይቀበሉ፣ በወጋገን ይመንዝሩ፣ በወጋገን ይሸለሙ” የውጭ ምንዛሪ ግኝት ማበረታቻ መርሀ-ግብር ለ1ኛ ዕጣ አሸናፊ አንድ ኪያ ስፖርቴጅ ዘመናዊ መኪና፣ ለ2ኛ ዕጣ አሸናፊዎች አምስት የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች እና ለ3ኛ ዕጣ አሸናፊዎች ደግሞ ሃምሳ ስማርት ሞባይል ስልኮች ማስረከቡ ይታወሳል፡፡ ወጋገን ባንክ በአሁኑ ወቅት በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ 397 ቅርንጫፎቹ ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ የኤሌክትሮኒክ ባንክ ፡- የኢንተርኔት እና ሞባይል ባንኪንግ አገልግሎቶች ፣ በኤቲኤም እና በክፍያ መፈፀሚያ ማሽኖች (ፖስ) የክፍያ ካርድ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

About the Author

Comments are closed.