የወጋገን ባንክ እያንዳንዱ አክሲዮን ያስገኘው ትርፍ ከ4.2 በመቶ ወደ 16.6 በመቶ አደገ

የወጋገን ባንክ እያንዳንዱ አክሲዮን ያስገኘው ትርፍ ከ4.2 በመቶ ወደ 16.6 በመቶ አደገ

አዲስ አበባ፣ህዳር 24 ቀን 2015 ዓ.ም:- ወጋገን ባንክ እ.ኤ.አ ሰኔ 30 በተጠናቀቀው የ2021/22 በጀት ዓመት ከነበረበት ዝቅተኛ አፈጻጸም ወጥቶ ተጨማሪ መጠባበቂያ ከተያዘ በኋላ ከታክስ በፊት ብር 572 ሚሊዮን ትርፍ አስመዝበ፡፡ ይህ ትርፍ ባንኩ በ2020/21 በጀት ዓመት ካስመዘገበው የብር 193 ሚሊዮን ትርፍ ጋር ሲነፃፀር የብር 379 ሚሊዮን ወይም 196 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡በመሆኑም እያንዳንዱ አክሲዮን ያስገኘው ትርፍ አምና ከነበረው 4.2 በመቶ ወደ 16.6 በመቶ አድጓል፡፡

ወጋገን ባንክ ህዳር 24 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ባካሄደው የባለአክሲዮኖች 29ኛመደበኛ እና 14ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብዲሹ ሁሴን ባቀረቡት እ.ኤ.አ የ2021/22 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት፣ባንኩ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተከስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት በትግራይ ክልል የሚገኙ 112 ቅርንጫፎቹ መዘጋት በአፈፃፀሙ ላይ ያሳደረበትን ከፍተኛ ጫና ተቋቁሞ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ 288 ቅርንጫፎች ብቻ እየሰራ ይህን ውጤት ማስመዝገቡ የሚያበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢው አቶ አብዲሹ ሁሴን ባንኩ እ.ኤ.አ በ2020/21 በጀት ዓመት ከነበረበት የአፈፃፀም መቀነስ ወጥቶ እ.ኤ.አ በ2021/22 ወደ ትርፋማነት ሊመለስ የቻለው የዳይሬክተሮች ቦርድ፣ ማኔጅመንቱና ሰራተኞች እንዲሁም ባለአክሲዮኖች ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ2021/22 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ ብር 33.9 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ካለፈው በጀት ዓመት ብር 31.5 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ8 በመቶ ወይም የብር 2.4 ቢሊዮን ዕድገት አሳይቷል፡፡ ባንኩ ለደንበኞች ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው ብድርም በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ ወደ ብር 30.3 ቢሊዮን ያደገ ሲሆን ካለፈው በጀት ዓመት ብር 27.3 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ11 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

በተመሳሳይ እ.ኤ.አ የ2020/21 በጀት ዓመት ብር 39.7 ቢሊዮን የነበረው የባንኩ ጠቅላላ ሀብት እ.ኤ.አ ሰኔ 30 በተጠናቀቀው 2021/22 የበጀት ዓመት የ9 በመቶ እድገት በማሳየት ብር 43.1 ቢሊዮን ደርሷል፡፡

ሰኔ 4 ቀን 1989 ዓ.ም በ16 ባለአክሲዮኖች በብር 60 ሚሊዮን የተፈረመ መነሻ ካፒታል እና በብር 30 ሚሊዮን የተከፈለ ካፒታል የተቋቋመው ወጋገን ባንክ በመላው ሀገሪቱ 400 ቅርንጫፎች ከፍቶ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የባንክ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት የባለአክሲዮኖቹ ቁጥር ከ7000 በላይ የደረሰ ሲሆን ከ5000 በላይ ሰራተኞች አሉት፡፡ባንኩ ሰኔ 4 ቀን 2014 ዓ.ም የተመሰረተበትን 25ኛ ዓመት በደመቀ ሁኔታ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች እና ሁነቶች ማክበሩ ይታወሳል፡፡

About the Author

Comments are closed.