ወጋገን ባንክ በ2019/20 የ47 በመቶ ዕድገት በማሳየት ከታክስ በፊት ብር 1.1 ቢሊዮን ብር ትርፍ አስመዘገበ

ወጋገን ባንክ በ2019/20 የ47 በመቶ ዕድገት በማሳየት ከታክስ በፊት ብር 1.1 ቢሊዮን ብር ትርፍ አስመዘገበ

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 22 ቀን 2013 ዓ.ም- ወጋገን ባንክ እ.ኤ.አ ሰኔ 30 በተጠናቀቀው የ2019/20 የበጀት ዓመት ከታክስ በፊት ብር 1.1 ቢሊዮን ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡ባንኩ ይህን ያስታወቀው ታህሳስ 22 ቀን 2013 ዓ.ም በሒልተን አዲስ አበባ ሆቴል ባካሄደው 27ኛ መደበኛ የባለአክሲዮኖች ጉባዔ ላይ ይፋ ባደረገው የኦዲት ሪፖርት ነው፡፡
የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ም/ሰብሳቢ አቶ ተፈራ ሞላ እንደተናገሩት ምንም እንኳን በበጀት አመቱ የኮሮና ባይረስ ወረርሽኝ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ላይ በፈጠረው መቀዛቀዝ ምክንያት በብድር አከፋፈል እና በደንበኞች ተቀማጭ ሂሳብ አሰባሰብ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ተከትሎ የብድር ወለድ ምጣኔ ቅናሽ የተደረገ ቢሆንም ፣ባንኩ በ2019/20 የበጀት ዓመት ከታክስ በፊት ብር 1.1 ቢሊዮን ትርፍ ያስመዘገበ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ይህም እ.ኤ.አ ከ2018/19 በጀት አመት አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር የ47 በመቶ ወይም የብር 342 ሚሊዮን ብልጫ እንዳለው አቶ ተፈራ ተናግረዋል፡፡
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ባንኩ የሰበሰበው የደንበኞች ተቀማጭ ገንዘብ በ2018/19 ከነበረው ብር 23.5 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ28 በመቶ ጭማሪ በማሳየት ወደ ብር 30.1 ቢሊዮን አድጓል፡፡ በባንኩ ደንበኞች የተከፈቱ የቁጠባ ሂሳቦች ብዛትም የ38 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 1.8 ሚሊዮን መድረሱን ምክትል ሰብሳቢው ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ባንኩ በተለያዩ የብድር ዘርፎች ለደንበኞች የሰጠው አጠቃላይ የብድር መጠንም በበጀት አመቱ መጨረሻ ላይ ብር 23.7 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ ካለፈው በጀት አመት አፈፃፀም ብር 16.5 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ44 በመቶ ጭማሪ አስመዝግቧል፡፡
አቶ ተፈራ አክለው እንደተናገሩት በ2019/20 የበጀት ዓመት የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ብር 2.9 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ጠቅላላ ካፒታሉም ወደ ብር 5.1 ቢሊዮን አድጓል፡፡ በተያያዘም የባንኩ አጠቃላይ ሀብት በ2019/20 ብር 38.2 ቢሊዮን መድረሱን ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል ባንኩ በ2019/20 በጀት ዓመት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች 43 ተጨማሪ ቅርንጫፎችን በመክፈት አጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ቁጥር በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 383 ማድረሱን ምክትል ሰብሳቢው ተናግረዋል፡፡በተመሳሳይ ባንኩ በኤሌክትሮኒክ ባንኪንግ አማካይነት ለደንበኞቹ የሚሰጠውን አገልግሎት ተደራሽነት ለማሳደግ፣ በመላው ሀገሪቱ 297 የኤቲኤም እና 273 የክፍያ መፈፀሚያ (ፖስ) ማሽኖችን በመትከል እንዲሁም የሞባይል፣ የኢንተርኔት እና የወኪል ባንክ አገልግሎቶችን ከማስፋት አንፃር መልካም አፈፃፀም ማስመዝገቡን ገልፀዋል፡፡
ማህበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንፃርም ባንኩ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በመንግስት የሚካሄዱ የልማት ሥራዎችን ለመደገፍ እና የኮሮና በሽታን ለመከላከል የሚደረገውን ሀገር አቀፍ ጥረት ለማገዝ ከብር 31 ሚሊዮን በላይ ድጋፍ ማድረጉ ታውቋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የባንኩ ባለአክሲዮኖች ቁጥር 3,998 የደረሰ ሲሆን፣ የባንኩ ሰራተኞች ቁጥር ደግሞ ባንኩን ወክለው በሚሰሩ ድርጅቶች ሥር የሚተዳደሩትን (Out sourced staff) ጨምሮ 7,709 ደርሷል፡፡

About the Author

Comments are closed.