ወጋገን ባንክ በ2012 በጀት ዓመት የ46.9 በመቶ ዕድገት በማሳየት ከታክስ በፊት ብር 1.1 ቢሊዮን ትርፍ አስመዘገበ

የፕሬስ መግለጫ ወጋገን ባንክ በ2012 በጀት ዓመት የ46.9 በመቶ ዕድገት በማሳየት ከታክስ በፊት ብር 1.1 ቢሊዮን ትርፍ አስመዘገበ
የወጋገን ባንክ ፕሬዝደንት አቶ አባይ መሐሪ የባንኩን የ2012 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም በተመለከተ በባንኩ ዋና መ/ቤት መግለጫ የሰጡ ሲሆን በመግለጫቸው እንደጠቀሱት ምንም እንኳ በበጀት ዓመቱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ላይ በፈጠረው መቀዛቀዝ ምክንያት በብድር አከፋፈልና የደንበኞች ተቀማጭ ሂሳብ አሰባሰብ ላይ አሉታዊ ተጽህኖ ያሳደረና ይህንንም ተከትሎ የብድር ወለድ ምጠኔ ቅናሽ የተደረገ ቢሆንም ባንኩ በ2012 በጀት ዓመት በሁሉም መመዘኛዎችና የሥራ ዘርፎች አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን ገልፀዋል፡፡ ባንኩ በ2012 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት ብር 1.1 ቢሊዮን ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን ይህም ውጤት ካለፈው ዓመት አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር የ46.9 በመቶ ወይም የብር 344.7 ሚሊዮን ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ በ2012 በጀት ዓመት የባንኩ የገቢ መጠን ብር 4.3 ቢሊዮን ሲደርስ ካለፈው የበጀት ዓመት የ34.1 በመቶ ብልጫ ማስመዝገብ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
አቶ አባይ መሐሪ ጨምረው እንደገለፁት በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የባንኩ አጠቃላይ የደንበኞች ተቀማጭ ሂሳብ መጠን ብር 30.1 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ካለፈው በጀት ዓመት ከነበረው ብር 23.5 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ27.8 በመቶ ዕድገት ወይም የብር 6.5 ቢሊዮን ጭማሪ ማሳየቱን ገልፀዋል፡፡ በጨማሪም፣ የባንኩ ደንበኞች ቁጥር 1.8 ሚለዮን መድረሱን አሳውቀዋል፡፡ ለደንበኞች በተለያዩ የብድር ዘርፎች የተሠጠው አጠቃላይ የብድር መጠንም በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ ብር 23.9 ቢሊዮን የደረሠ ሲሆን ካለፈው በጀት ዓመት አፈፃፀም ብር 16.5 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ45 በመቶ ጭማሪ ማስመዝገቡን አስረድተዋል፡፡ ባንኩ በ2012 በጀት ዓመት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች 42 ተጨማሪ ቅርንጫፎችን የከፈተ ሲሆን በበጀት ዓመቱ መጨረሻም የቅርንጫፎቹን ብዛት 382 ማድረስ መቻሉን ፕሬዝደንቱ አስታውቀዋል ፡፡ በተመሳሳይ፣ ባንኩ የኤሌክትሮኒክስ ባንኪንግ አገልግሎቱን በሰፊው ለማዳረስ እንዲችል በመላ ሀገሪቱ 297 የኤቲ ኤምና 273 ፖስ ማሽኖችን በመትከል እንዲሁም የሞባይልና የኢንተርኔት አገልግሎቶችን በስፋት በመስጠት በዘርፉ ቀዳሚ ባንክ ለመሆን እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የባንኩ የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚዎች ቁጥር 575 ሺህ እንዲሁም የኤጀንሲ ባንኪንግ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር 116 ሺህ መድረሱን ፕሬዝደንቱ አስታውቀዋል፡፡
በተያያዘም፣ የባንኩ ፕሬዝደንት አቶ አባይ መሐሪ ባንኩ የማህበራዊ ሀላፊነቱን ለመወጣት ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጋር ለመስራት ስላቀደው ሥራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫቸው እንደጠቀሱት፣ ወጋገን ባንክ በተለያዩ ወቅቶች በጤናና ማህበራዊ እንዲሁም በተፈጥሮና ሠው ሠራሽ አደጋዎች የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት ከተለየዩ አካላት ጋር እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀው ባንኩ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጋር በተለያዩ ዘርፎች አብሮ ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሱን ገልፀዋል፡፡ አቶ አባይ መሐሪ ወጋገን ባንክ ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደረገበትን ቼክ ለማህበሩ ፕሬዝዳንት ባስረከቡበት ወቅት እንደገለፁት ባንኩ የማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እንዲችል ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የተለያዩ ድጋፎችን የሚያደርግ ሲሆን በየዓመቱም ለማህበሩ የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንዲሁም የብር 50 ሺህ ዓመታዊ የአባልነት መዋጮ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም ከ4900 በላይ የሆኑትን የባንኩ ሠራተኞችና የማኔጅመንት አባላትን በማስተባበር ለማህበሩ በየወሩ ቋሚ ወርሃዊ መዋጮ እንዲያደርጉ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ ማህበረሠቡም የአቅሙን በማዋጣት ማህበሩን መርዳት እንዲችል የባንክ አካውንት በመክፈትና በባንኩ ቅርንጫፎች የሙዳይ ሣጥኖች በማስቀመጥ የማህበሩን የገንዘብ አቅም ለማሳደግ ድጋፍ እንደሚደረግ የባንኩ ፕሬዝደንት ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም፣ የባንኩ ፕሬዝደንት ይህ አመርቂ ውጤት እንዲመዘገብ አስተዋጾ ላደረጉት ለሚመለከታቸው የመንግሰት አካላት በተለይም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ለዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ ለባንኩ ባለአክስዮኖች፣ ለባንኩ ደንበኞች፣ ለሠራተኞችና ለማኔጅመንት አባላት ከፍ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

About the Author

Leave a Reply