ወጋገን ባንክ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ሆኖ ትርፍ አስመዘገበ

ወጋገን ባንክ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ሆኖ ትርፍ አስመዘገበ

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 16 ቀን 2014 .:- ወጋገን ባንክ እ.ኤ.አ ሰኔ 30 በተጠናቀቀው የ2020/21 የበጀት ዓመት በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ያጋጠመው የኢኮኖሚ መዳከም፣ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተከሰተው ግጭት እና እሱን ተከትሎ በመልካም ስሙ ላይ የደረሰበት የስም ማጥፋት ዘመቻ በሥራ እንቅስቃሴው ላይ ከባድ ጫና ቢያሳድርበትም ፤በእዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ሆኖ ትርፍ አስመዘገበ፡፡

ወጋገን ባንክ ታህሳስ 16 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ባካሄደው የባለአክሲዮኖች 28 መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብድሹ ሁሴን ባቀረቡት ዓመታዊ የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት እንደገለፁት በትግራይ ክልል በተከሰተው ግጭት ምክንያት በአካባቢው የሚገኙ በርካታ ቅርንጫፎች ለረጅም ጊዜ ከሥራ ውጪ በመሆናቸው፣ከክልሉ ሲገኝ የነበረው ከፍተኛ ተቀማጭ ገንዘብ ሳይሰበሰብ በመቅረቱ፣በአካባቢው ተሰጥቶ የነበረው ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር በጊዜው መሰብሰብ ባለመቻሉ ምክንያት የባንኩ የተበላሸ ብድር መጠን ከፍ ብሏል፡፡ በዚህም ምክንያት ባንኩ ከትርፉ ተቀናሽ በማድረግ ከፍተኛ መጠባበቂያ ገንዘብ እንዲይዝ ተገዷል፡፡ይህም የባንኩን ዓመታዊ የትርፍ መጠን እንደቀነሰው የቦርድ ሰብሳቢው ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በተሳሳተ የሚዲያ ዘገባ ምክንያት በባንኩ ላይ የደረሰው የስም ማጥፋት ዘመቻ፣እያደገ የመጣው የዋጋ ንረት፣ከፀጥታ ችግሮች ጋር ተያይዞ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መቀዛቀዝና የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መስፋፋት በበጀት ዓመቱ የባንኩን የሥራ እንቅስቃሴ በማስተጓጎል አፈፃፀሙ ዝቅ እንዲል ማድረጉን አቶ አብድሹ ሁሴን ተናግረዋል፡፡ይሁንና ካቀደው አንፃር የሥራ አፈፃፀሙ ዝቅ ያለ ቢሆንም ያጋጠሙትን ፈታኝ ተግዳሮቶች ተቋቁሞ በበጀት ዓመቱ ባንኩ ከታክስ በፊት ያስመዘገበው የብር 193.1 ሚሊዮን ትርፍ አበረታች ሊባል የሚችል መሆኑን የቦርድ ሰብሳቢው ገልፀዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ2019/20 የበጀት ዓመት ብር 2.9 ቢሊዮን የነበረው የባንኩ የተከፈለ ካፒታል በ2020/21 ወደ ብር 3.3 ቢሊዮን ያደገ ሲሆን ጠቅላላ ካፒታሉ ብር 5 ቢሊዮን ደርሷል፡፡ ባለፈው የበጀት ዓመት ብር 38.2 ቢሊዮን የነበረው ጠቅላላ ሀብቱም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ወደ ብር 39.7 ቢሊዮን አድጓል፡፡

ወጋገን ባንክ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንፃር በንቃት የሚሳተፍ ሲሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከብር 33 ሚሊዮን በላይ ወጪ በማድረግ የማህበራዊ ኃላፊነት ግዴታዎችን ከመወጣት አንፃር የተለያዩ የበጐ አድራጐት ስራዎች በገንዘብ አግዟል፡፡ ለአብነትም በአዲስ አበባ ከተማ ድጋፍ የሚሹ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ማሟያና ምገባ እንዲሁም ለኮሮና ቫይረስ መከላከል ሥራ በገንዘብ ያደረጋቸዉ ድጋፎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መንግስት የሚያካሂዳቸውን የልማት ፕሮጀክቶች በመደገፍ ረገድ ለገበታ ለሸገር ፕሮጀክት ብር 5 ሚሊዮን እና ለገበታ ለአገር ፕሮጀክት ብር 10 ሚሊዮን ያደረጋቸው ድጋፎች ከብዙ በጥቂቱ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በመላው ሀገሪቱ 399 ቅርንጫፎች ያሉት ወጋገን ባንክ ከ5000 በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የባለአክሲዮኖቹ ቁጥር ከ4000 በላይ ደርሷል፡፡ ወጋገን ባንክ በቅርንጫፎቹ ከሚሰጠው መደበኛ የባንክ አገልግሎት በተጨማሪ የአሌክትሮኒክ ባንኪንግ ማለትም የክፍያ ካርድ በኤቲኤም እና በግብይት መፈፀሚያ ማሽኖች (ፖስ) እንዲሁም የኢንተርኔት፣ የሞባይልና የኤጀንት ባንኪንግ አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት በመስጠት አገልግሎቱን ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ ችሏል፡፡

ሰኔ 4 ቀን 1989 ዓ.ም በ16 ባለአክሲዮኖች በብር 60 ሚሊዮን የተፈረመ መነሻ ካፒታል እና   በብር 30 ሚሊዮን የተከፈለ ካፒታል የተቋቋመው ወጋገን ባንክ በያዝነው ዓመት እ.ኤ.አ. ሰኔ 11 ቀን 2022 25 ዓመት ይሞላዋል፡፡ ይህንን ክብረ በዓልም በተለያዩ ክንውኖች በማክበር ላይ ይገኛል፡፡

About the Author

Comments are closed.