ወጋገን ባንክ የ25ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን አከባበር የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት አካሄደ  ለኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል የ1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

ወጋገን ባንክ የ25ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን አከባበር የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት አካሄደ ለኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል የ1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ጥቅምት 18— ቀን 2014 ዓ.ም- ወጋገን ባንክ የ25ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን አከባበር የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት በባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ እና የሥራ አመራር አባላት፣ሰራተኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በዛሬው ዕለት አካሄደ፡፡

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብድሹ ሁሴን በበዓሉ መክፈቻ ሥነ-ሥርአት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ወጋገን ባንክ ባለፉት 25 ዓመታት የባንክ አገልግሎት ባልተዳረሰባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች አገልግሎቱን ተደራሽ በማድረግ በርካቶችን የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ከማድረጉም በላይ ለአገሪቱ የባንክ ዘርፍ እድገት የጎላ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡ባንኩ ከህረተሰቡ የሰበሰበውን ተቀማጭ ገንዘብ መልሶ ወደኢኮኖሚው ፈሰስ በማድረግና የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን በማበረታታት እንዲሁም የወጪ ንግድን በመደገፍ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን አቶ አብድሹ ሁሴን ተናግረዋል፡፡በተጨማሪም ከ5,000 ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን አቶ አብድሹ ሁሴን ጨምረው ተናግረዋል፡፡
በዕለቱ ወጋገን ባንክ የ25ኛ አመት የምስረታ በዓል አከባበሩን ይፋዊ መክፈቻ ምክንያት በማድረግ ለኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል በልብ ህመም ለሚሰቃዩ ህፃናት ህክምና የሚውል የብር 1,000,000.00 (አንድ ሚሊዮን ብር) የበጎ አድራጎት ድጋፍ ማድረጉን የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብድሹ ሁሴን ተናግረዋል፡፡
አቶ አብድሹ ሁሴን የድጋፍ ቼኩን ለማዕከሉ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ህሩይ አሊ ካስረከቡ በኋላ እንደተናገሩት ወጋገን ባንክ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተከሰተው የሠላም መደፍረስ በሥራ እንቅስቃሴው ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል የፈጠረበት ቢሆንም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ሆኖ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በልብ ህመም እየተሰቃዩ ህክምና ለማግኘት ተራ የሚጠብቁ በርካታ ህፃናት መኖራቸውን በመረዳት የማዕከሉን የተቀደሰ ዓላማ ለማገዝ የገንዘብ ልገሳ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ወጋገን ባንክ የ25ኛ ዓመት የምስረታ በአሉን ለቀጣይ ስምንት ወራት በተለያዩ ሁነቶች ማለትም በበጎ አድራጎት ሥራዎች፣ለመሰል አገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ፣ለደንበኞች እና ረጅም አመት ላገለገሉ ሰራተኞች የዕውቅና ፕሮግራም በማዘጋጀት፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችና በሌሎችም ዝግጅቶች በደመቀ ሁኔታ የሚያከብር ይሆናል፡፡ወጋገን ባንክ ላለፉት 25 አመታት በመላ ሀገሪቱ የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል የሚካሄዱ የልማት ሥራዎችን በመደገፍና በሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ሥራዎችን በገንዘብ በማገዝ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ሲወጣ የቆየ ባንክ ነው፡፡
በ16 ባለሀብቶች በብር 60 ሚሊዮን የተፈረመ መነሻ ካፒታል እና በብር 30 ሚሊዮን የተከፈለ ካፒታል ሰኔ 4 ቀን 1989 ዓ.ም የተመሠረተው ወጋገን ባንክ በአሁኑ ወቅት የባለአክሲዮኖቹ ቁጥር ከአራት ሺህ በላይ የደረሰ ሲሆን ሰራተኞቹን ጨምሮ ከሁሉም የአገራችን ህብረተሰብ ዜጎች አክሲዮን ገዝተው የባንኩ ባለቤት ሆነዋል፡፡ እ.ኤ.አ ሰኔ 30 ቀን 2021 የተከፈለ ካፒታሉ ብር 3.2 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ጠቅላላ ካፒታሉ ወደ ብር 5.5 ቢሊዮን አድጓል፡፡ የባንኩ አጠቃላይ ሀብትም ከብር 40 ቢሊዮን በላይ ሆኗል፡፡ወጋገን ባንክ በአሁኑ ወቅት በመላው ሀገሪቱ 398 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን በቅርቡ በዘርፉ ተወዳዳሪና ስኬታማ ሆኖ ለመቀጠል የሚያስችለውን የአምስት አመት ስትራተጂክ እቅድ ነድፎ በሥራ ላይ ያዋለ ሲሆን እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ አዲስ መዋቅር አዘጋጅቶ ለደንበኞቹ ቀልጣፋና አርኪ አገልግሎት ለመስጠት እየተጋ ነው፡፡

About the Author

Comments are closed.