ወጋገን ባንክ “በወጋገን ይቆጥቡ ፣ በወጋገን  ይሸለሙ ”በሚል ስያሜ ላካሄደው የሎተሪ ዕጣ መርሃ-ግብር አሸናፊዎች ሽልማታቸውን አስረከበ

ወጋገን ባንክ “በወጋገን ይቆጥቡ ፣ በወጋገን ይሸለሙ ”በሚል ስያሜ ላካሄደው የሎተሪ ዕጣ መርሃ-ግብር አሸናፊዎች ሽልማታቸውን አስረከበ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 26 ቀን 2013 ዓ.ም ፡-ወጋገን ባንክ ከጥቅምት 1 እስከ መጋቢት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ “በወጋገን ይቆጥቡ፤ በወጋገን ይሸለሙ ” በሚል ስያሜ ሲያካሂድ ለቆየው የቁጠባ ማበረታቻ መርሀግብር የሎተሪ ዕጣ አሸናፊዎች ሽልማቶቻቸውን ዛሬ ግንቦት 26 ቀን 2013 ዓ.ም የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ እና ከፍተኛ የስራ አመራር አባላት እንዲሁም የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ተወካዮች በተገኙበት በባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት ባካሄደው ደማቅ ሥነ-ሥርዓት በይፋ አስረከበ፡፡
ሚያዝያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር አዳራሽ በይፋ በወጣው ዕጣ መሰረት የ1ኛ ዕጣ አንድ ዘመናዊ የቤት አውቶሞቢል አሸናፊ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል የቤንች ማጂ ከተማ ነዋሪው አቶ አዲሱ ስዩም ሲሆኑ የ2ኛ ዕጣ ሁለት ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች አሸናፊዎች ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወ/ት ስንታየሁ በላይ እና የመቀሌ ከተማ ነዋሪው አቶ ግርማይ መላኩ ናቸው፡፡ የ3ኛ ዕጣ 20 የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች ፣የ4ኛ ዕጣ 30 ባለ 32 ኢንች ኤል ኢዲ ቴሌቪዥኖች እና የ5ኛ ዕጣ 40 ስማርት ሞባይል ስልኮች ዕድለኞች ደግሞ በተለያዩ ሀገሪቱ ክፍሎች ባሉት አሥሩም የወጋገን ባንክ ዲስትሪክት ፅ/ቤቶች ሥር የሚገኙ ቅርንጫፎች ደንበኞች ናቸው፡፡

የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ብርቱካን ገብረእግዚ ሽልማቶቹን ለዕድለኞች በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት በወጋገን ይቆጥቡ ፣በወጋገን ይሸለሙ የቁጠባ ማበረታቻ መርሐ-ግብር የባንኩን የቁጠባ መጠን ከፍ በማድረግ እና የገበያ ድርሻውን ከማሳደግ ብሎም ባንኩ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚያቀርበውን ብድር ከመጨመር አንጻር አበረታች አስተዋፅኦ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ የሎተሪ ሽልማት ፕሮግራሙ የባንኩን መልካም ገጽታ በመገንባት፣ ከደንበኞቹ ጋር ያለውን ትስስር የበለጠ ከማጎልበት እና ተጨማሪ ደንበኞችን ከመሳብ አንፃርም የራሱን ጉልህ ሚና መጫወቱን ወ/ሮ ብርቱካን አክለው ተናግረዋል፡፡

ወ/ሮ ብርቱካን ጨምረው እንደገለፁት በዛሬው ዕለት በሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ሽልማቶቻቸውን የተረከቡት 19 ዕድለኞች ሲሆኑ ለቀሪዎቹ ዕድለኞች ባንኩ በአቅራቢያቸው በሚገኙ ቅርንጫፎቹ በኩል ሽልማቶቻቸውን ባሉበት እንደሚያስረክብ አስታውቀዋል፡፡

ወጋገን ባንክ በአሁኑ ወቅት በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ 397 ቅርንጫፎቹ ከሚሰጠው የተሟላ የባንክ አገልግሎት በተጨማሪ የኢንተርኔት እና ሞባይል ባንኪንግ አገልግሎቶች ፣ በኤቲኤም እና በክፍያ መፈፀሚያ ማሽኖች (ፖስ) የክፍያ ካርድ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ወጋገን ባንክ በአሁኑ ወቅት 2,241,863 ደንበኞች ያሉት ሲሆን የባለአክሲዮኖቹ ቁጥርም 4,056 ደርሷል፡፡

About the Author

Comments are closed.