ወጋገን ባንክ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

ወጋገን ባንክ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

መጋቢት 24 ቀን 2012 ዓ.ም  በሠላም ሚኒስቴር ቅጥር ግቢ በተካሄደው የድጋፍ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው የእርዳታውን ቼክ ለብሔራዊ የድጋፍ አሰባሰብ ኮሚቴ  ያስረከቡት የወጋገን ባንክ  የኮርፖሬት ሰርቪስስ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ክንዴ አበበ “ሁልጊዜም በሀገሪቱ የሚካሄዱ የልማት ስራዎችን በመደገፍና የተፈጥሮም ሆኑ ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሲከሰቱ  ለወገን ደራሽነቱን በማረጋገጥ የማህበራዊ ኃላፊነቱን ሲወጣ የቆየው ወጋገን ባንክ በሀገራችን ላይ የህልውና አደጋ የደቀነውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመግታት የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት በማገዝ በዚህ አስቸጋሪ የፈተና ወቅት ከህዝባችን ጎን መቆም እንዳለብን በመገንዘብ የብር 5 ሚሊዮን ድጋፍ አድርገናል” ብለዋል፡፡

 

አቶ ክንዴ አበበ  ጨምረውም  “ወጋገን ባንክ  የኮሮና ቫይረስን የመከላከሉ ተግባር  ውጤታማ እስኪሆን ድረስ ከመንግስትና ከህብረተሰቡ ጎን ሆኖ ድጋፉን የሚቀጥል መሆኑን እየገለፅኩ፤ ሁላችንም ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደ አንድ ሆነን በትብብር ከሰራን በሽታውን የከፋ ጉዳት ሳያደርስ እንደምንቆጣጠረው  ባለሙሉ ተስፋ ነኝ” ብለዋል፡፡

 

ወጋገን ባንክ እንደ አንድ ኃላፊነት የሚሰማው ተቋም የቫይረሱን ሥርጭት ለመከላከል በዋናው መስሪያ ቤትም ሆነ በየቅርንጫፎቹ ለሰራተኞቹና ለደንበኞቹ ስለበሽታው መተላለፊያና መከላከያ መንገዶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በማከናወን  የእጅ መታጠቢያ ቁሳቁሶችን እና የፅዳት እቃዎችን እያቀረበ መሆኑን የገለፁት አቶ ክንዴ አበበ በሥራ ቦታ ያለውን  አካላዊ ጥግግት ለመቀነስም ለሰራተኞቹ ፈቃድ በመስጠት፣ በተለይም ለነፍሰጡር ሰራተኞች ከአመት ፈቃዳቸው የማይታሰብ ረፍት በመስጠት የሰራተኞቹን ደህንነት ለመጠበቅ ባንኩ  ተግቶ እየሰራ መሆኑን  ተናግረዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

በተጨማሪም በሽታውን ለመከላከል ቁልፍ የሆነውን አካላዊ መራራቅ ለመተግበር፣ ደንበኞች ወደ ቅርንጫፍ መምጣት ሳያስፈልጋቸው በሥራ ቦታቸው ወይም በቤታቸው ሆነው የኤሌክትሮኒክ ባንክ አገልግሎቶችን በመጠቀም ሂሳባቸውን ማንቀሳቀስ የሚችሉ  ሲሆን በአጋር ካርዳቸው በኤቲኤም ማሽን ብቻ በመጠቀም ወደሚፈልጉት  ሰው ሒሳብ ገንዘብ መላክ እና በቀን እስከ 10,000 ብር ማውጣት ፣በስልክዎ ባንክዎ የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት በቀን እስከ 50,000  ብር ማስተላለፍ  እና  የግለሰብ ኢንተርኔት ባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች በቀን እስከ 100,000  ብር ፣ድርጅቶች ደግሞ የሚፈልጉትን ያህል ገንዘብ በኮርፖሬት ኢንተርኔት ባንክ አገልግሎት ማስተላለፍ የሚችሉ መሆኑን ባንኩ  አስታውቋል፡፡

 

ለተጨማሪ መረጃ፡- ማርኬቲንግና ኮርፖሬት ኮሚኒኬሽንስ ዳይሬክቶሬት፣ራስ መኮንን ጎዳና  አዲስ አበባ ስታዲየም ፊት ለፊት 14ኛ ፎቅ

ስልክ.+251 11 878 7921/19

About the Author

Leave a Reply