ወጋገን ባንክ የ25ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለሁለት የበጎ አድራጎት ተቋማትና ለአንድ ትምህርት ቤት የብር 825,150 የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

ወጋገን ባንክ የ25ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለሁለት የበጎ አድራጎት ተቋማትና ለአንድ ትምህርት ቤት የብር 825,150 የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11 ቀን 2014 ዓ.ም- ወጋገን ባንክ የ25ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ለሁለት የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ለአንድ ትምህርት ቤት ብር 825,150 በዓይነት እና በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
ባንኩ ለዋይድ ሆራይዘን ፎር ችልድረን ኢንኮርፖሬሽን የተሰኘ በኢትዮጵያ የተመዘገበ ወላጅ አልባ ህፃናትን በመርዳት ላይ ለተሰማራ ምግባረ ሰናይ ድርጅት ብር 225,000.00 ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፣ የተቸገሩ ወላጆችና ህፃናትን ለሚረዳው ሙዳይ የተሰኘ አገር በቀል የበጎ አድራጎት ማህበር ደግሞ ብር 230,150 የሚያወጡ የተለያዩ የምግብ ግብአቶችን ለግሷል፡፡
በሌላ በኩል ለኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 የወይራ ቅድመ አንደኛና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ግምቱ ብር 370,000 የሚያወጣ የተማሪዎች መመገቢያ ጠረጴዛና መቀመጫ ወንበር ድጋፍ ማድረጉን ባንኩ አስታውቋል፡፡
በድጋፍ አሰጣጡ ሥነ-ሥርአት ላይ ተገኝተው የድጋፍ ቼኩን እና የቁሳቁስ እርዳታውን ያስረከቡት የወጋገን ባንክ የፋይናንስ እና ማቴሪያልስ ማኔጅመንት ዋና መኮንን እና የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አክሊሉ ውበት ተወካይ አቶ የኋላሸት ዘውዱ ወጋገን ባንክ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንፃር ባለፉት አመታት በትምህርት እና በጤና ዘርፍ እንዲሁም የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡

በተለይም ከመጋቢት 2010 ዓ.ም እስከ የካቲት 2014 ዓ.ም ድረስ ባሉት አራት አመታት ብቻ በመላው ሀገሪቱ ለጤና፣ ለትምህርት ፣ በሰው ሰራሽና ተፈጥሮ አደጋዎች ለተፈናቀሉ ዜጎች መልሶ ማቋቋሚያ እንዲሁም በክልሎች እና በፌደራል ደረጃ የተካሄዱ የልማት ሥራዎችን ከብር 70 ሚሊዮን በላይ ወጪ በማድረግ መደገፉን አቶ የኋላሸት ተናግረዋል፡፡
ለአብነት ያህልም ለኦሮሚያ ክልል የብር 10 ሚሊዮን፣ ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የብር 10 ሚሊዮን፣ ለገበታ ለሸገር ብር 5 ሚሊዮን ፣ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ተግባር ብር 5 ሚሊዮን፣ለሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ በፊስቱላ ለተጠቁ እናቶችና ልጃገረዶች ህክምና የሚውል ብር 500,000 እንዲሁም ለኢትዮጰያ የልብ ህሙማን መርጃ ማዕከል በልብ ህመም ለተጠቁ ህፃናት ህክምና ያደረገው ብር 1,000, 000 (አንድ ሚሊዮን) ባንኩ ካደረጋቸው ድጋፎች መካከል በምሳሌነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን አቶ የኋላሸት ተናገረዋል፡፡የአሁኑ ድጋፍም ባንኩ ይህንኑ አጠናክሮ ለመቀጠል ባለው የፀና እምነት የ25ኛ ዓመት የምስረታ በአሉን አስመልክቶ የተደረገ መሆኑን አቶ የኋላሸት ጨምረው ተናግረዋል፡፡
ባንኩ በቀጣይም በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ በሚያደርጉና የህብረተሰቡን ቁልፍ ማህበራዊ ችግሮች በመፍታት ተግባር ላይ ለተሰማሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መሰል ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

ባንኩ በመላው ሀገሪቱ በከፈታቸው 400 ቅርንጫፎች ከሚሰጠው መደበኛ የባንክ አገልግሎት በተጨማሪ የኤሌክትሮኒክ ባንኪንግ ማለትም፡- የክፍያ ካርድ በኤቲኤምና በግብይት መፈፀሚያ ማሽኖች (ፖስ) እንዲሁም የኢንተርኔትና የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
የተመሰረተበትን 25ኛ ዓመት በተለያዩ ሁነቶች እያከበረ የሚገኘው ወጋገን ባንክ በአሁኑ ጊዜ ከ5,000 በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን የባለ አክሲዮኖቹ ቁጥር ከ5,500 በላይ ሆኗል፡፡
በአሁኑ ወቅት የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ብር 3.4 ቢሊዮን ሲሆን ጠቅላላ ካፒታሉ ደግሞ ብር 5.6 ቢሊዮን እንዲሁም ጠቅላላ ሀብቱ ከብር 41.2 ቢሊዮን በላይ ነው፡፡

About the Author

Comments are closed.